የገቢ ማስገኛ መርሃ ግብሩ የተሳካ መሆኑ ተገለጸ

ሚያዚያ 23 2003 ከቀኑ 5፡30 ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አዳራሽ ለተገኘ ሰው ዛሬ ምን ተፈጥሮ ነው ሰዉ ሁሉ እንዲህ ተፍ ተፍ የሚለው ያስብላል። እናቶችና እህቶች የምግብ ማዘጋጃ ክፍሉን ተቆጣጥረውታል። ከፊሉ ወጣቶች አዳራሹን ሲያስውቡ ከፊሎቹ ደግሞ የቪዲዮ ፣ የድምፅ ፣ የፕኦጀክተር እንዲሁም ዝግጅቱን ለመላው አለም ለማስተላለፍ የሚረዷቸውን ኮምፒተሮች መልክ መልክ ያሲዛሉ። የመርሐ ግብሩ ሰዓት ደርሶ ከዲሲ እና አካባቢው የተጋበዙ እንግዶች ሲገኙ አዳራሹ አምሮና ሰምሮ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ብዙ ሩጫ የነበረበት አይመስልም። ብፁዓን አባቶች፣ የደብር አስተዳዳሪዎች፣ ካሕናት አባቶችና ዲያቆናት ቦታቸውን ከያዚ በኃላ ጉባኤው በብፁዕ አቡነ ገብርኤል በፀሎት ተከፍቶ በኮሚቴው ሰብሳቢ የሥራ እንቅስቃሴ ሪፓርት ቀረበ ፤ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ እስጢፋኖስ ባህሩና በብፁዕ አቡነ አብርሃም የዲሲና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ መልከ ጼዴቅ በሕይወት በቆዩበት ጥቂት አመታት ለቤተክርስቲያን ስላበረከቱት መንፈሳዊ፣ ማሕበራዊ እና የልማት እንቅስቃሴዎች ትንታኔ ከተሰጠ በኋላ የገቢ ማሰባሰቢየ ዝግጅት በቀሲስ ዘበነ እና በመምህር ሕዝቂያስ ተከናውናል።

በጉባኤው ላይ የነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ እጅግ የሚያስደንቅ እና እውነትም ብጹዕነታቸው አንድ ጠይቀው ሁለት የሚያገኙ ናቸው የተባለውን ቃል እንድናስታውስ አርጎናል። የዝክረ መልከ ጼዴቅ ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ የሆኑት ቆሞስ አባ ፈቃደ ኢየሱስ ዝግጅቱን አስመልክቶ አነጋግረናቸው እንደገለጹልን ዝግጅቱ እጅግ ከተጠበቀው በላይ የተሳካ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም በወንድማቸው በብጹዕነታቸው እረፍት እጅግ በጣም እንዳዘኑ በማስታወስ አሁን ከዚህ ዝግጅት በኋላ ምን ተሰማዎት ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ ሲመልሱ በፊትም ብጹዕነታቸው በአካል ስለተለዩን ሳይሆን በየቦታው ተሰርቶ የማያልቅ የሚመስል ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ጀምረው ፤ ልጆችን ለማሳደግ በየቦታው ሰብስበው በመሔዳቸው የተሰበሰበው ይበተናል፤ የተስተካከለው ይበተናል ነበረ ሀዘኔ። አሁን ብጹዕነታቸው “እኔ እግዚአብሔር ያመለከተኝን እጀምራለሁ የሚያስፈጽሙትን ደግሞ እሱ ያስነሳል” እንዳሉት ይኸው ብዙዎችን አስነስቷል ከእንግዲህ ወዲህ ሀዘን የለም ሥራዎችን በአግባቡ ማስፈጸም እንጂ ብለዋል። በመጨረሻም በዝግጅቱ አስፈላጊውን ሁሉ ላበረከቱ ምዕመናን በእግዚአብሔር ስም ምስጋና አቅርበዋል።

This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.